Popular Posts

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ71ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰብዓዊ መብቶች ቀን በማስመልከት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ከሚሰሩ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች የተሰጠ መግለጫ
+++++++++++++++++++++++++++++++++++
ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እኤአ ዲሴምበር 8 ቀን 1948  ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights (UDHR) ማጽደቁ ይታወሳል፡፡ ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንደ መለኪያ የሚያገለግለው ይህ ሰነድ፣ የሰው ልጆችን የማይገሰስ ክብር እውቅና የሰጠ ሲሆን እነዚህም መብቶች ለዓለም ፍትህ፣ ነጻነት እና ሠላም መሰረቶች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡  በሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 2 ላይ ማንም ሰው በዘር፣ በሃይማኖት፣ ጾታ፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ፖለቲካዊ አቋም፣ ማህበራዊ መነሻ፣ ዜግነት ወይም ሌላ ማናቸውም ምክንያት ያለምንም ልዩነት ሁሉንም መብቶች እና ነጻነቶች የተጎናጸፈ መሆኑንም እውቅና ይሰጣል፡፡

ዘንድሮ የሚከበረውን 71ኛውን የሰብዓዊ መብቶች ቀን ልዩ የሚያደርገው ከዚህ ቀደም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ተጥሎባቸው የነበረው ማእቀብ ተነስቶ፣ መንግስትም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁርጠኝነቱን ባረጋገጠበት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በትብብር ለመስራት እርምጃ በጀመሩበት ማግስት መሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከህዳር 25 - 30 ቀን 2012 ዓ.ም የሰብዓዊ መብቶች ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ሰንብቷል፡፡ ዛሬ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም የሚደረገው የመዝጊያ ፕሮግራምን በማስመልከት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የምንሰራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚከተለውን መልዕክት ማስተላለፍ እንወዳለን፡፡

ስለሆነም ስማችን ከዚህ በታች የተጠቀሰው 6 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ኮሚሽኑ፣

1. ኢትዮጵያ ተቀብላ የህገ-መንግስቷ አካል ያደረገቻቸውን ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና ስምምነቶች ከመላው ዓለም የሰው ልጆች ሁሉ ሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች የዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር በሚጣጣም መልኩ እንዲከበሩ፣ እንዲስፋፉ እና እንዲሟሉ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንደምንቀጥል እናሳውቃን፡፡ 
2. በሀገራችን የመጣውን የለውጥ እቅስቃሴ ተከትሎ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የሚያግዘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሻሻሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱበት የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ እና የምርጫ ቦርዱ በአዲስ መልክ መዋቀሩ እና በአንጻራዊ መልኩ የፕሬስ ነጸነት መከበሩ አወንታዊ እርምጃዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ለውጦችም ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብን ለመፍጠር መሰረት እነደሚጥሉ እምነታችን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት መንግስት የጀመራቸው ተግባራት ለሰብዓዊ መብቶች መሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እናምናለን፡፡
3. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የደረሰው የህይወት መጥፋት፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ የአካል ጉዳቶች፣ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና መሰል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተባባሱ መምጣታቸው የመንግስት የህግ ማስከበር እና የፍትህ ጥያቄዎችን የመመለስ አቅም እየተፈታተኑ ዜጎችን ለከፋ የሰብዓዊ መብት ቀውስ እያጋለጡ በመሆኑ የሚመለከታቸው የህግ አስከባሪ አካላት ባስቸኳይ በመብቶች ጥሰት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች እና ተቋማትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡ 
በዚህም መሰረት፡- 

I. የፌዴራል መንግስት
++++++++++++++++

1. ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት ረገድ ያሉበትን ዓለም ዓቀፍ ግዴታዎች እንድወጣ፣ ለዚህም የህግ የበላይነትን በማስፈን ለዜጎቹ ተገቢውን ጥበቃ እንድያደርግ፣ 
2. ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች ስምምነቶች አንጻር መንግስት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድወስድ፣ ሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊ መሆን እንዲችሉ የህግ ማስከበር ሃላፊነቱን እንዲወጣ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች የሚካሱበትን እና የመብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ በህግ አግባብ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት እንዲያጠናክር፣ ለዚህም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እንዲሰራ፣
 
II. የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች
++++++++++++++++++++++++

1. ለሁሉ ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እና ኢትዮጵያ ለፈረመቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ተገዥ በመሆን በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተሳታፊዎችን በማጣራት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርጉ፣ ዜጎች በማንኛውም አካባቢ ተዘዋውረው የመኖር እና የመስራት መብታቸውን እንዲያስከብሩ፣ 
2. የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን ማስተዋወቅ እንዲችሉ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ዜጎች ፖለቲካዊ እና የመደራጀት መብታቸውን እንዲጠቀሙ አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ፣

III. የፖለቲካ ፓርቲዎች
++++++++++++++++++
1. የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች መከበር እና የዲሞክራሲ ባህል መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ፣ ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከቱ ያሉባቸውን ግዴታዎች እንድያከብሩ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች በማስፋፋት በማክበር እና በማስከበር በትጋት እንዲሰሩ፣ 
2. የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን በሚያስተዋውቁበት እና ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ከማናቸውም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት እና ንግግሮች እንዲቆጠቡ፣ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሰለጠነ ውይይት እና ክርክር በማድረግ በፍሬ ነገር ጉዳዮች ላይ አማራጭ በማቅረብ ለዜጎች ፕግራሞቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንድያስተዋውቁ፣

IV. ወጣቶች
+++++++++++
1. የዚህ ዓመት የሰብዓዊ መብቶች ቀን ወጣትነት ለሰብዓዊ መብቶች በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡ የማህበረሰብ እንቅስቃሴዎች ለፍትህ፣ ነጻነት እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋና ተዋናዮችም ወጣቶች እንደመሆናቸው፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች መከበር ዋና ተዋናይ መሆን እንድችሉ፣  
2. በሠላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ በተለያዩ ማህራበዊ ጉዳዮች ላይ የመወያየት እና የመከራከር ልምድን በማዳበር ለሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች መከበር፣ መስፋፋት እና መፈጸም ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የውይይት ባህል እንዲያዳብሩ እንጠይቃለን፡፡

ሠብዓዊ መብቶች ለሁሉም!

1. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
2. ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ 
3. የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት 
4. የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ 
5. ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች  
6. የህግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች - ኢትዮጵያ
7. የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር

#CEHRO

No comments:

Post a Comment

Featured Post

Ragaa MEDIA: Sutuumee yaa sutuumee Maal jaajjata Kottuu mee - Sayyoo Dandanaa @Ragaa MEDIA

Sutuumee yaa sutuumee Maal jaajjata Kottuu mee - Sayyoo Dandanaa @Ragaa MEDIA Ragaa MEDIA is the home old and non archived music, songs and...